ጃይካ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እንደሚደግፍ አስታወቀ

ሚያዚያ 21/2014 (ዋልታ) የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (JAICA) ምርትና አገልግሎት ያላቸውን ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እንደሚደግፍ አስታወቀ፡፡

በጃይካ የዋናው መስሪያ ቤት ከፍተኛ አማካሪ ልዑካን ቡድን አባላት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ልዑካኑ በኬኒያ፣ በሩዋንዳ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በዘርፉ የሰሯቸውን ስራዎችና ተሞክሮዎችን ያካፈሉ ሲሆን “ቀጣይ ኢኖቬሽን ከጃፓን ጋር” (Next Innovation with Japan – NINJA) የተሰኘውን ፕሮጀክት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ምርትና አገልግሎት ያላቸውን ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችና የግል ዘርፍ ኢንዱስትሪን መደገፍ፣ ድርጅቶች እንዲስፋፉ ማድረግና የአቅም ግንባታ መስጠትን የሚያካትት ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ከግብ እንዲደርስ በከፍተኛ ጥረትና ትብብር ወደ ስራ እንዲገባ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ እና የጃፓንን የረጅም ጊዜ ትብብር ያነሱት ሚኒስትሩ፣ ጃይካ እና የጃፓን ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ የዘርፉን ስራ እንዲያግዙ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡