ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በኬኒቺ ኦህኖ (ፕ/ር) ከተመራ የጃፓን ልማት የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ልኡክ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አተገባበር ያለበት ደረጃ፣ ውጤቱ እና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት ስለ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አተገባበር እና የታለመላቸውን ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ ሚኒስትሯ ለልዑኩ አብራርተዋል።
ይህ እቅድ የተሳካ እንዲሆን በዋነኝነት ሀገር በቀል እውቀት እና ክህሎትን ለማጎልበት እንደሚሠራ ገልፀዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ከውጭ ሀገራት ስለሚገኙ ድጋፎችን አስፈላጊነት አንስተዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተለይ እንደ ጃፓን ዓይነት የዓለማችን አገራት ያለፉበትን ሂደት ማየት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ይፋ ከምታደርገው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ጋር በተገናኘም ምርትን በማሳደግ፣ በሰው ሃብት፣ በተቋም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በተሳካ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ትግበራ ዙርያ ከጃፓን ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ጠቅሰዋል።
ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ የልኡኩ አባላት ከኢንዱስትሪ ፖሊሲ ትግበራ ጋር በተገናኘ ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ፍላጎት መግለፃቸውን ያመለክታል።