ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በሰላም አስተምህሮ ላይ በጋራ መስራት እንደምትፈልግ ገለጸች

የካቲት 11/2014 (ዋልታ) የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በሰላም አስተምህሮ ላይ በጋራ መስራት እንደምትፈልግ ጃፓን ገለጸች፡፡

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ቨኢቶ ታካኮ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እና የተፈናቀሉ ዜጎችን ሰብኣዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ እስከ አሁን በተሰሩ እና ቀጣይ በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው አገራቸው ጃፓን በቀውስ ጊዜ ሥራ አስተዳደር ሰፊ ልምድ ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰው የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር በሰላም አስተምህሮ ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩንና የሰብኣዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሂደቱን ለመደገፍ የጃፓን መንግሥት ያለውን ፍላጎትና ዝግጁነት መግለፃቸውንም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡