ጃፓን የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ትደግፋለች ገለፀች

የካቲት 10/2014 (ዋልታ) ጃፓን የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ታካኮ ገለፁ።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ታካኮ ዛሬ የጃፓን ብሔራዊ ቀን መታሰቢያን በኢምባሲያቸው ሲያከብሩ ጃፓንና ኢትዮጵያ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰብኣዊ መብትና በሕግ የበላይነት ማስፈን በሚሉት እሴቶች ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው ብለዋል።

በቅርቡም የጃፓን ዓለም ዐቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በዴሞክራሲና በምጣኔሃብት እድገት ጃፓን ያላትን ልምድ ለማጋራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚሁ ስኬት በቅርቡ ጃይካ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጉዳዩ ላይ ሥምምነት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባትና ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ጃፓን እንደምትደግፍ ነው ያረጋገጡት።

ጃፓን በተለይም በሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ልምድ ማካበቷን ገልፀው ኢትዮጵያ በመስኩ ለበርካታ ዓመታት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል።

ጃፓንና ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆኑን አንስተው በተለይም በችግር ወቅት እርስ በእርስ የተደጋገፉ አገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ጃፓን ኢትዮጵያ በምጣኔሃብትና በፖለቲካው መስክ ለምታከናውነው ተግባር ድጋፎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደሯ አረጋግጠዋል።