አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ አረፉ

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) “ጃፓኗን ወድጄ” በሚል እውነተኛ ታሪካቸው የተዘፈነላቸውና የባለብዙ ታሪክ ባለቤቱ አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ አረፉ፡፡
አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ በሰሜን ሸዋ ቡልጋ አውራጃ በ1926 ተወለዱ፡፡
ከዛም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እድገታቸውና የልጅነት ጊዜያቸዉን ያሳለፉት ደግሞ ላምበረት ሾላ አካባቢ ነበር፡፡
በኋላም በ1940 ዓ.ም የክብር ዘበኛ ሰራዊትን ተቀላቅለዋል፡፡ ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ በ1942 ዓ.ም የአንደኛው ቃኘዉ ዘማች ሆነው እንዲሁም በ1944 ዓ.ም በሶስተኛዉ የቃኘው ዘመቻ ሁለት ጊዜ ወደ ኮሪያ ዘምተዋል፡፡
ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላም በክብር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ዉስጥ ተቀጥረው እያገለገሉ እያለ በ1954 ዓ.ም ከወ/ሮ የሽመበት ወለደማሪያም ጋር ጋብቻ መስርተው 8 ወንዶችና 3 ሴቶች በድምሩ 11 ልጆችን አፍርተዋል፤14 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
በ1974 ከክብር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ጡረታ ከወጡ በኋላ በግላቸው የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ ሂወታቸዉን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡
አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ እሩቅ ምስራቅ በነበሩበት ወቅት ከአንዲት ጃፓናዊት ጋር ጓደኝነት መስርተው ነበርና ወደ ሃገር ቤት ሲመለሱ እውነተኛ ታሪካቸዉን “ሩቅ ምስራቅ ሳለሁ ጃፓኗን ወድጄ” የሚለውን ግጥም ራሳቸው፣ ዜማውን ደግሞ ከሌሎቹ ጋር በትብብር አሰናድተው ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ባማረ ሁኔታ እንደተጫወተው ልጃቸው እየሩሳሌም ሸዋንዳኝ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በክቡር ጥላሁን ገሰሰ የተዜመው “ስትሄድ ስከተላት” አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ከአሁኑ ባለቤታቸውና ከልጆቻቸው እናት ጋር የነበረውን ሁኔታ የገለጹበት ግጥማቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ለብዙነሽ “እንዲህ ነው ጋብቻ” ፣ለጋሽ ማሃሙድ ደግሞ “ፍቅር በዘበዘኝ” የሚሉ ግጥሞችን ሰርተዋል፡፡
ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ጃፓኗን ወድጄ በሚል የዘፈነላቸው አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ትናንት ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ህይወታቸው ማለፉንና ቀብራቸው በነገው እለት በአዲስ አበባ የካ ሚካኤል ከቀኑ 9፡00 እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡