ጅማ ዩኒሸርሲቲ በግንባር የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ለተዘጋጁ የጤና ባለመያዎች አሸኛኘት አደረገ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – የጅማ ዩኒሸርሲቲ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት በግንባር የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በራሳቸው ተነሳሽነት ለተዘጋጁ 11 የጤና ባለሙያዎችን አሸኛኘት አደረገ።

ኢንስቲትዩቱ ለጤና ባለሙያዎቹ አሸኛኘት ያደረገው ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ካላቸው የህክምና ቁሳቁሶች ጋር ነው።

የጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩቱ ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ኤልያስ ዩሱፍ  እንዳስታወቁት፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው የህልውና ዘመቻ ምክንያት በአካባቢው ያለው  የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለማገዝ  11 የጤና ባለሙያዎች  ወደ ስፍራው ተሸኝተዋል።

ከጤና ባለሙያዎቹ ጋር  20 የህክምና አልጋዎችንና ሌሎች የመገልገያ ቁሶች ተልከዋል።

የጤና ባለሙያዎች የሀገር አርበኞች ናቸው ያሉት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ ናቸው።

ሀገርንና ወገንን የማዳን ተሳትፎ ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው አቅም የራሳቸውን ሃላፊነት መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ባለሙያዎቹ  አገልግሎት ለመስጠት በራሳቸው ተነሳሽነት ያሳዩት ተሳትፎ ጀግናና ቆራጥ ናችሁ፣ ምስጋና ይገባቸዋልም ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሲስተር ሰብለወጌል ገለታ ከዘማች የጤና ባለሙያዎች መካከል አንዷ ስትሆን  ሰራዊታችንን  በሙያዬ ለማገልገል እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ብላለች፡፡

ሀገር ሳትፈልግ የገባችበትን ጦርነት በሙያችን   ለማገልገል በቁርጠኝነት ተነስተናል ስትልም አክላለች።

ሌሎቹም ዘማች የጤና ባለሙያዎች  በፍላጎታቸው ተነሳሰተው በሙያቸው  የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡