ጆ ባይደን በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት 100 ሚሊየን ሰዎችን ለመከተብ ማቀዳቸውን ገለጹ

አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ስልጣን በመጡ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት 100 ሚሊየን ሰዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ ግብ አስቀምጠው እየሰሩ መሆናቸው ገልጸዋል።

ባይደን አክለውም ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ የስልጣናቸው ወራት ወረርሽኙን ማጥፋት ከባድ እንደሚሆን ባይክዱም ክትባቱ እንዴት እንደሚከፋፈልና ጉዳቱ እንዴት መቀነስ እንደሚቻል እቅድ አዘጋጅተናል ብለዋል።

ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ጥር ወር ላይ ስራ የሚጀምረው የጤና ቡድናቸውን በሚያስተዋውቁበት ሰአትም አሜሪካውያን ለመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ትናንት ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ፋይዘር/ባዮንቴክ የሚያመርተው ክትባት ለአሜሪካውያን መከፋፈል እንዲጀመር የሚረዳ አንድ ሪፖርት መውጣቱ ደግሞ በበርካቶች ዘንድ ተስፋን አጭሯል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮቪድ ክትባት ፕሮግራማቸውን በተመለከተ ዋይት ሀውስ ውስጥ ስብሰባ ያካሄዱ ሲሆን፣ በቅርቡ ፈቃድ ይሰጠዋል የተባለውን ክትባት ፍጥነት አድንቀዋል ተብሏል።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት አሜሪካ እስካሁን ድረስ 15 ሚሊየን ሰዎች በኮሮረና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ 285 ሺህ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ይህ ቁጥር በአለማችን ከፍተኛው ነውም ተብሏል።

በአሁኑ ሰአት በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች እንደ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ወደ ሆስፒታሎች እየገቡ ስለመሆናቸው ቢቢሲ ዘግቧል።