መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም እድሜያቸው እስከ 3 ዓመት ለሆኑ ሕፃናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡
ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ 40 ሚሊዮን ብር በጀት የያዘ ሲሆን በመጀመሪው ዙር የአልሚ ምግብ ድጋፍ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በተለዩ ዘጠኝ ሺሕ እናቶችና ህፃናት የሚጀመር ነው ተብሏል፡፡
ቀጥታ ድጋፉን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተመረጡ 32 የኅብረት ሥራ ሸማቾች ማኅበር ሱቅ በየወሩ በኩፖን እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ዛሬ ከተማዋ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው የልጀነት ዘመን እንክብካቤ የእድሜ ዘመን ጤንነት፣ የትምህርት ውጤታማነት እንዲሁም በሥራ ዓለም እና በህይወት ዘመን የሚመጣ ስኬትን እንደሚያጎናፅፍ ተናግረዋል፡፡
የህጻናት አእምሮ በተገቢው መንገድ ብሩህ ሆኖ መጎልበት ቻለ ማለት በነገ ሀገር ግንባታ ሥራ ላይ ቀጥተኛ የሆነ በጎ ተጽእኖ ያመጣል ያሉት ምክትል ከንቲባው ከተማ አስተዳደሩ በህፃናትና በእናቶች ጤንነት ላይ አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው አሊ የኅብረት ሥራ ሸማቾች ሱቅ የሕዝብ አገልጋይ እንደመሆናቸው መጠን በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በኃላፊነት እንደሚወጡ መናገራቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።