“ገዚያ” የዳውሮ ሴቶች የነፃነት ቀን ተከበረ

ጥቅምት 9/2014 በዳውሮ ዞን ኢሰራ ወረዳ የዳውሮ ሴቶች የነፃነት ቀን “ገዚያ” በዓል በድምቀት ተከበረ።

አዲስ ዓመት በገባ በሰባተኛ ሳምንት ማክሰኞ በሴቶች ብቻ በትልቅ ዛፍ ስር በድምቀት የሚከበር የሴቶች የነፃነት ቀን በዓል ዘንድሮም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተለያዩ መርኃግብሮች ተከብሯል።

የዳውሮ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ዳዕሞ ደስታ የገዚያ በዓል ተጠብቆ እንዲቆይና በማይዳሰሱ ቅርስ እንዲመዘብ የዘርፉ ባለሙያዎች የተለያዩ ጥናቶችን ማድረግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

የዞኑ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ እንዳለ ሀ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ በዓሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በበዓሉ ማጠናቀቂያ ላይ የሚተከሉ ዛፎችና መድሃኒትነት ያላቸው እጽዋት የአካባቢን ስነ ምህዳር ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው መግለጻቸውን ከዳውሮ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዓሉ የሴቶችን እኩልነትና ነፃነትን ከማክበር ባለፈ ሴቶች በአካባቢያቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር ሀገር በቀል እውቀት ነውም ተብሏል፡፡