ጉባኤው በኢትዮጵያ የተቃጣውን ጫና በመቃወም ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የተቃውሞ ደብዳቤ ሊልክ ነው

ኅዳር 24/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የተቃጣውን ጫና በመቃወም ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የተቃውሞ ደብዳቤ ሊልክ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ደብዳቤው በሰብዓዊነት ሽፋን የአገሪቱን ወቅታዊ ችግርን በማወሳሰብ ተግባር ላይ የተሰማሩ መንግስታት እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ካሉት ሁለንተናዊ ጫና እንዲታቀቡ ለማሳሰብ ያለመ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

የተቃውሞ ደብዳቤው ለተባበሩት መንግስታት፣ ለዓለም ዐቀፍ የሃይማኖት ተቋማት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለአሜሪካ መንግሥት እና ኤምባሲ፣ ለሲቪክ ማህበራት እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በመላክ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም እውነታውን ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያስተላልፉ እንዲሁም እየበረታ የመጣውን ጫና ለመቀልበስ እንዲያግዝ ይጠይቃል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ከአንዳንድ የምዕራባውያን አገራት የሚደረገው ጫና እና እጅ ጥምዘዛ በሀገር ሉዓላዊንት እንዲሁም በዜጎች ክብር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በማስገንዘብ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ለመጠየቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ የጥፋት እጃቸውን የዘረጉ ምዕራባውያን አገራትን ለመቃወም ያለመ ነውም ተብሏል::

በሄብሮን ዋልታው