ጋዜጠኛ ሄርሜላ የትግራይ እውነተኛ ጀግኖች የሕዝብን ደኅንነት በማሰብ ከመንጋ አስተሳሰብ የወጡ ናቸው አለች

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ

ጥር 8/2014 (ዋልታ) ከትግራይ ክልል የበቀሉ እውነተኛ ጀግኖች የሕዝብን ደኅንነት በማሰብ ከመንጋ እሳቤ የወጡ ናቸው ስትል ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገለፀች፡፡

የትግራይ ተወላጅ እውነተኛ ጀግኖች ከመንጋ አስተሳሰብ ለመውጣት ድፍረት የኖራቸውና የሕዝባቸውን ደኅንነት በማሰብ ከሽብር ቡድኑ ትሕነግ የጥፋት መንገድ ራሳቸውን የነጠሉ እንደሆኑ ነው የጠቆመችው።

‹‹ስለ ፖለቲካ ቡድኖች ያለዎትን አስተሳሰብ ለመለወጥ ነፃ ነዎት›› ያለችው ሄርሜላ ይህ ደግሞ ‹‹ያን ያክል ከባድ አይደለም፤ ሰዎች ሃይማኖትን ቀይረውም ጭምር ይኖራሉ እኮ›› ስትል ነው አያሌ አማራጮች ባሉበት ዓለም ውስጥ ትሕነግ ‹ከእኔ ውጭ ኅልውና የለህም› በሚል የሚሰብከውን የትግራይ ሕዝብ እንዲነቃ የጠቆመችው።

የመንግሥትን የወደ አገር ቤት ጥሪ ተቀብላ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የሲቢኤስ ጋዜጠኛና የበቃ #nomore ዘመቻ አስተባባሪ ሄርሜላ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ባቀረበቻቸው ጥሪዎች የትግራይ ተወላጆች ከአሸባሪው ትሕነግ የጥፋት መንገድ ይልቅ ከእውነትና ከሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ስትጠይቅ ከርማለች፡፡