መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) ግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ያገኛቸውን 80 ተሽከርካሪዎች ለክልሎች ግብርናና መሬት አስተዳደር ቢሮዎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና በፌደራል ደረጃ ለሚገኙ ተጠሪ ተቋማት ድጋፍ አደረገ፡፡
በመስኖ ስንዴ ልማት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡትን ለማበረታታትና በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ለማቋቋም እና በተለያዩ ሁኔታዎች የተሽከርካሪ ድጋፍ ለሚፈልጉ ክልሎችና ተቋማት ነው ድጋፉ የተደረገው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን የተሸከርካሪ ድጋፉ በዋናነት የተጀመረውን የመስኖ ስንዴ ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠልና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም ነው።
የመሬት አስተዳደር ሥራዎችን በተለይ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ሰርቲፍኬት በማጠናቀቅ አርሶ አደሮች ከፋይናንስ ተቋማት የመበደር ዋስትና እንዲኖራቸው በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ሥራን ማስቀጠልና በሌሎችን ጥሩ አፈፃፀም ያላቸውን ዞኖችና ወረዳዎች ለማነቃቃት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በክልሎች ካለው ችግር አኳያ ትንሽ ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ ከማድረግ አኳያ ተሽከርካሪዎቹን በአግባቡ በመጠቀም ግብርናን ለማሻገር ለሚሰሩ ስራዎች ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።
መሰል ድጋፎች ለሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች ወደ ፊት እንደሚጥል የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።