ግብጽና ሱዳን የውሃ ሙሌት ሂደቱን እንዲታዘቡ ብጋበዙም መጥተን አናይም ማለታቸው የህዳሴ ግድቡ እንደማይጎዳቸው ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው – መምህር እንዳለ ንጉሴ

ሚያዝያ 07 ቀን 2013 (ዋልታ) – “ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የውሃ ሙሌት አስቀድማ ግብጽና ሱዳን ሂደቱን እንዲታዘቡ ብትጋብዝም አገራቱ መጥተን አናይም ማለታቸው የህዳሴ ግድብ እንደማይጎዳቸው ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ  የዲፕማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ ገለፁ።

በፈረንጆቹ 2015 በተቀመጠው መርህና አካሄድ መሰረት ውሃ ከመሙላቷ በፊት የሦስቱም አገራት ባለሙያዎች ተገኝተው አመኔታቸውን እንዲሰጡ የተቀመጠውን ስምምነት በማክበር የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

መምህር እንዳለ  እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛው የግድቡ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ አስቀድሞ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል አገራቱ እንዲታዘቡ ባለሙያዎች እንዲልኩ ጥሪ ማድረጓ ከሞራል፣ ከሕግና ከዝግጅት አንፃር ትክክለኛ አካሄድ ነው።

“ወደፊት እነርሱም የሚሠሩትን ለኢትዮጵያ ማሳየት አለባቸው ያሉት መምህሩ፤ ግን ይህ ስለሚያሰጋቸው ማሳየት አይፈልጉም፣ ዲፕሎማሲውም በተሳካ መልክ መሄዱም ያሳፍራቸዋል፣ ለህዝባቸው ብዙ የዋሹት ስላለና ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ደግሞ ማጠናቀቂያውም ስለሚሆን ፈርተውታል” ብለዋል መምህሩ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሁለቱን አገራት ባለሙያዎች እንዲታዘቡ መጋበዟ ግዴታ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በፈረንጆቹ 2015 በተቀመጠው መርህና አካሄድ መሰረት ውሃ ከመሙላቷ በፊት የሦስቱም አገራት ባለሙያዎች ተገኝተው አመኔታቸውን እንዲሰጡ የተቀመጠውን ስምምነት በማክበር የተደረገ ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ የምትገነባው ግድብ ቢሆንም ጥሪ ማድረጓም በመርህ የምታምን ከመሆኗም በላይ የ2015 የመርህ ስምምነትን መሰረት በማድረግ ግዴታና ሃላፊነቷን ለመወጣት ያደረገችውን ጥረት እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

ተግባሩ ስምምነቱን ማክበሯን፣ በሞራልም ሆነ በዲፕሎማሲው ዘርፍ መምራቷን እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ዘንድ ትልቅ ከበሬታን ያስገኝላታል ብለዋል። እነርሱ አስዋንንም ሆነ ሌሎች ግድቦቻቸውን ሲገነቡ ግን ኢትዮጵያን እንዳልጠሩም አስታውሰዋል።

መምህሩ አክለውም በዲፕሎማሲው ዓይን ሲታይ  ‹‹ኢትዮጵያ የሠራሽው ልክ ነው። በቃ ሙይው እንደማለት ይቆጠራል። እኛ ማጭበርበርም መዋሸትም አልቻልንም ስለዚህ የዋሸነው ህዝባችን ዓይናችንን ከሚያወጣው አይሆንም ብለን ብንቀር ይሻላል›› ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።