ግብጾች በዓባይ ዙሪያ ካካሄዷቸው ዓለም አቀፍ ጥናቶች አንዱም ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ አይደለም -ፕሮፌሰር አደም ካሚል

ፕሮፌሰር አደም ካሚል

መጋቢት 10/2013 (ዋልታ) – ግብጾች ዓባይን የተመለከቱ 560 ጥናቶችን ያካሄዱ ሲሆን፣ አንዳቸውም ፍትሐዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ላይ ያተኮረ እንዳልሆነ የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አደም ካሚል አመለከቱ።

ከአዲስ ዘመን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ ያደረጉት ፕሮፌሰር አደም በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ቀውሶችና ግጭቶች የግብጽ እጅ እንዳለበት የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ ግብጾች ዓባይን የግላቸው ማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

የግብጽ ዋነኛ የጥናትና የምርምር ሥራዎቻቸው ማጠንጠኛ ዓባይና ኢትዮጵያ መሆናናቸውን የጠቀሱት ፕሮፌሰር አደም፣ እስካሁንም ዓባይን የተመለከቱ አለም አቀፍ 560 ጥናቶች ያካሄዱ ሲሆን አንዳቸውም ፍትሐዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትን የሚያሳዩ አለመሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የሱዳን ምሁራንም ደጋግመው የሚሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያን በቀና መንገድ እንደማያይዋት እንደሚያሳይና ለአብነትም ፕሮፌሰር ሀሰን መኪ የተባለ የሱዳን ምሁር ‹‹የኢትዮጵያ መጠናከር ለሱዳንም ሆነ ለአካባቢው አገራት አደጋ ነው›› በሚል በግልጽ በአደባባይ ሲናገር መደመጡን አስታውሰዋል፡፡

ግብጽ ለአንድ ቀንም እንኳን እጇን ከኢትዮጵያ ላይ አንስታ አታውቅም፤ ዘወትር ኢትዮጵያን ለማዳከም ስትሰራ ኖራለች ሲሉም አክለዋል፡፡