መጋቢት 08/2013 (ዋልታ) – ግብፅ እና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በአረቡ ሀገራት እና በምዕራባዊያኑ ዘንድ የፕሮፓጋንዳ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ገልጸዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና የዲፕሎማሲው ጦርነት ነው ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች ብዙ ቢሆኑም የተቀናጀ ስራ አለመሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
የዲፕሎማሲውን ግንኙነት ለማሻሻል እና እውነታውን ለአለም ህዝብ ለማሳወቅ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ሌሎች ተቋማት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ሁለቱ የተፋሰሱ ሀገራት ከስምምነት ይልቅ ዛቻ እና ማስፈራራትን መምረጣቸው በኢትዮጵያ ላይ የሉዓላዊነት መደፈር እና መሰል ችግሮች እየደረሰባት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሂደት 79 በመቶ የደረሰ ቢሆንም፤ ግድቡን ለማጠናቀቅ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዶ/ር አረጋዊ፣ ይህንንም ለማሳካት በህብረት እና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
(በብርሃኑ አበራ)