ጠላት በጥላቻ ታውሮ ሀገር ለማፍረስ ቢጥርም እኛ ግን በመስዋዕትነትና በፍቅር እንገነባታለን – ጠ/ሚ ዐቢይ

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) ጠላት በጥላቻ ታውሮ ሀገር ለማፍረስ ቢጥርም፤ እኛ ግን በመስዋዕትነት እና በፍቅር እንገነባታለን ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1443ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ዋዜማን ወልዲያና አካባቢው ከሚገኘው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እያከበሩ ይገኛሉ።

መላው የእስልምና እምነት ተከታዮችን እንኳን ለ1443ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋዜማውን ከሠራዊቱ አባላትና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በማክበራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

ጠላት ኢትዮጵያን ስለሚጠላ ዋጋ ከፍሎ ይሞታል፤ እኛ ግን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ስለምንወድ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ እንከፍላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቼም ቢሆን በጥላቻ ታውሮ አገር ማፍረስ አይቻልም ብለዋል፡፡

እኛ ግን በፍቅር እንገነባታለን፤ ይህንንም ሠራዊቱ በተግባር አረጋግጧል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገዳደሩን ፈታኞቻችን ቢተባበሩና ቢበረቱም እኛን ግን እያስተማሩና እያጠናከሩን ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል።

በዋዜማ ክብረ በዓሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ እና የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋሲካ በዓል ዋዜማን በሰቆጣና አካባቢዋ ነዋሪዎችና የሠራዊቱ አባላት ጋር ማክበራቸው ይታወሳል፡፡

አስታርቃቸው ወልዴ (ከወልዲያ)

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!