ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር በመዝመት አገርን ለማዳን ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን የሚመዘገብ ነው

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ግንባር በመዝመት አገርን ለማዳን ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን የሚመዘገብ ነው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

ፓርቲዎቹ ወደ ግንባር በመዝመት የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

የአገሪቷ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አገር ከተቃጣባት የኅልውና አደጋ ለመታደግ ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና ታሪክ የማይረሳው እንደሆነም አመልክተዋል።

የትግራይ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) እንደ ፓርቲ አገርን ከሚበታትን የኅልውና አደጋ ለመታደግ በሚያስፈልገው ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንቆማለን ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ የሕወሓት የሽብር ቡድንና ሌሎች ተላላኪዎች በአገር ላይ እያሳደሩ ያለውን ጫና በጋራ መመከት አገራዊ ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ፓርቲያቸው አገርን ለማዳን በሚደረገው ማንኛውም ተግባር በጋራ ለመስራትና ለኢትዮጵያ ኅልውና መጠበቅ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ቁርጠኛ አቋም ማስቀመጡን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር በመሰለፍ የኅልውና ዘመቻውን ለመምራት መወሰናቸው ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በኅልውና ዘመቻው በመሳተፍ ኢትዮጵያን ለማዳን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዩታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የህዝብ  ግንኙነት ኃላፊ መጋቤ ብሉይ አብርሃም ናቸው።

”ኢህአፓ ኢትዮጵያን የማዳን ጽኑ አቋም አለው” ያሉት ኃላፊው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል የኅልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ለቋመጡ አካላት ትምህርት መስጠት እንደሚገባ  አመላክተው፤ “በድል ተመልሰን ለዓለማቀፍ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗን እናሳያለን” ብለዋል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰይፈስላሴ አያሌው (ዶ/ር) ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የኅልውና አደጋ ለመመከት በሚደረገው ጥረት ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ሂደት ቀያሪና የአድዋ ድልን ለመድገም እድል ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን! ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡