ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላለፉ

ጥቅምት 14 /2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በድጋሚ የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ዋና ፀሀፊ ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያልዎት መልዕክት አስተላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሺ ጂንፒንግ ዳግም መመረጥ የቻይናን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የፕሬዝዳንቱን ውጤታማ የአመራር ብቃት ያረጋግጣል ብለዋል።

ሺ ጂንፒንግ በአመራር ዘመናቸው የቻይናን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማስቀጠል ባለፈ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን በማሳደግ በኩል ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም ጠቅላይ ሚኒትሩ በመልክታቸው አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም የቻይናን ኮሚዩኒስት ፓርቲ ሀገር በቀል የልማት ሞዴልን ጠቃሚነት አሁን ላይ እንደሚረዳ እምነቴ ነው ብለዋል።

ሺ ጂንፒንግ በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በዜጎች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ ያደረጉት ያልተቋረጠ ጥረት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ጥሩ ተሞክሮና ትምህርት ነው ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ከፓርቲው በርካታ ልምዶችን ቀስማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም በሰው ተኮር ልማት፣ በውጤታማ አስተዳደር እና በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከን እንዴት ሕዝብ ተኮር አገልግሎት መስጠት፣ በጋራ ማደግ እና ሀገርን በታማኝነት ማገልገልን በተመለከተ መልካም ተሞክሮ መውሰዷን አውስተዋልል፡፡

በሺ ጂንፒንግ አስተዳደር ቻይና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

የሺ ጂንፒንግ ዳግም መመረጥም የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ከቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡