ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ2017 የዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጳጉሜን 5/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ2017 የዘመን መለወጫ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለ2017 የዘመን መለወጫ በዓል ዕንቁጣጣሽ በዓል አደረሳችሁ

ዘመን ዕድል ነው፡፡ ዘመንን መጠቀም ግን የሥራ ውጤት ነው፡፡ ዘመንን ፈጣሪ ለሁላችንም በእኩልነት ሰጥቶናል፡፡ ልዩነት የሚፈጠረው በዘመን በመሥራትና ባለመሥራት ነው፡፡ በታሪካችን ውስጥ የምንኮራባቸው ምእራፎች አሉ፡፡

በሕይወታችን ውስጥም ደስ የሚያሰኙን ጊዜያት አሉ፡፡ እነዚያ ምእራፎችና ጊዜያት ሌላ ነገር አይደሉም፡፡ የተሰጠንን የዘመን ዕድል በሚገባ ተጠቅመን የሠራንባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡

እኛ ብንፈልግም ባንፈልግም ዘመን ይለወጣል፡፡ ጊዜ ወደፊት ብቻ የሚሄድ ማሽን ነውና፡፡ ማንም አያስቆመውም፤ አቅጣጫም አያስቀይረውም፡፡ የሚቻለው በጊዜ መጠቀም ብቻ ነው፡፡ “ክረምት ለሰነፍ ገበሬ መዓት፤ ለጎበዝ ገበሬ ምሕረት ነው” ይባላል፡፡ ምሕረትና መዓቱ ከዝናቡ የሚመጣ ሳይሆን ከገበሬዎቹ ዝግጅትና ሥራ የሚገኝ ነው፡፡ በሰነፍ ገበሬ ላይ ዘመን ይለወጥበታል፤ ብርቱው ገበሬ ግን ዘመንን ራሱን ይለውጠዋል፡፡

በ2016 ለኢትዮጵያ ምን አሳክተናል? በ2017ስ ለኢትዮጵያ ምን ተዘጋጅተናል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የዘመን መለወጥን ትርጉም ይቀይረዋል፡፡ ዘመን እየተለወጠብን ነው ወይስ ዘመኑን እየለወጥነው ነው? የሚለውን ያመለክተናል፡፡ ኢትዮጵያን ዘመን እየለወጣት ብዙ ጊዜ ኖራለች፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ በብርታትና በትጋት ዘመኑን ለውጣው ታውቃለች፡፡ ዘመን ሲለውጠን፣ ከተራራ እንደተፈነቀለ ድንጋይ፣ ወዳሰብነው ሳይሆን ወደ ፈለገው ነው የሚወስደን፡፡

2017 የሚለውጠን ሳይሆን የምንለውጠው ዓመት እንዲሆን ነው ምኞቴ፡፡ ዕቅዶቻችንን ተግብረን፤ ፕሮጀክቶቻችንን በጊዜና በጥራት አጠናቅቀን፤ ግጭቶቻችንን በውይይትና በድርድር ፈትተን፤ የዘመናት ስብራቶቻችንን በምክክርና በሽግግር ፍትሕ ጠግነን፤ በብዙ ነገሮች ራሳችንን ችለን፤ ሪፎርሞቻችንን በብቃት አሳክተን፣ የምንለውጠው ዘመን እንዲሆን ነው ምኞቴ፡፡

2017ን በኢትዮጵያ ታሪክ የሚጠቀስ ዘመን ለማድረግ እንዘጋጅ፡፡ የዘመናት ዕዳዎቻችን የምናወራርድበት፤ የኖሩ ቁስሎቻችን የምናክምበት፤ የዘመናት ሕልሞቻችንን ሥር መሠረት የምናስይዝበት፤ የታሪክን መኪና መሪና ማርሽ የምንቆጣጠርበት ዘመን ለማድረግ እንነሣ፡፡

ወደፊት የሚመጡት ልጆቻችን “ይሄ ታሪክ የተሠራው፣ የዛሬ ስንት ዓመት በ2017 ነው” እንዲሉን እናድርገው፡፡

በወጀብና በዐውሎ ውስጥ አስገራሚ ሥራዎችን እንድንሠራ የፈቀደ ፈጣሪ ዛሬም ከእኛ ጋር ነው፡፡ ነገም ከእኛ ጋር ነው፡፡ መሥራት የእኛ ማከናወንም የእርሱ ነው፡፡ እኛ ከተነሣን ዘመኑን እንድንለውጠው እርሱ ይረዳናል፡፡

በድጋሚ እንኳን ለ2017 የዘመን መለወጫ በዓል ዕንቁጣጣሽ አደረሳችሁ
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጳጉሜን 5፣ 2016 ዓ.ም