ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ከተማ አቀፍ ምክክር ተጀመረ


ግንቦት 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የምክክር ምዕራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አስጀምሯል።

በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተጀመረው ከተማ አቀፍ የምክክር ምዕራፍ የህብረተሰብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ፣ የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ፈተናዎቹ ሳይበግሩት ለብዙ ዓመታት ብዙዎች ሲመኙት የነበረውን መቀራረብንና መግባባትን ለማምጣት ስራውን እያከናወነ ለዚህ ደረጃ በቅቷል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስዳደር አጀንዳ እንደሚሰበስብና በአማራና በትግራይ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡

የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች ብዙ ተምሮ የተሻለ የሰላምና የእድገት ውርስ ይተዋል የሚል እምነት ኮሚሽኑ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡

ከስብራት ህይወት ወጥተን ወደ ተሻለ ህይወት እንሸጋገር ዘንድ ወጣቱ ችግሩን በአጀንዳ ቀረፃ ጠብመንጃውን ወደ ሐሳብ መንጃና ማንሸራሸሪያ እንዲቀይር ኮሚሽኑ በትህትና ይጠይቃል ማለታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የሀገራችን ችግር ወደ ሀገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደት የሰላም በር በየትኛውም ቦታ ላሉ ወገኖች እንዲመቻች ጠንክሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳውን በግልም ሆነ በጋራ ወደ ኮሚሽኑ ማምጣት እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ ምክክሩ አካታች እንደሚሆንና ሂደቱም ግልፅና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንደሚከወን አረጋግጠዋል፡፡