ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሸባሪውን ሸኔ ሕዝቡ ለምን ተሸከመው የሚለውን መጠየቅ ይገባል አሉ

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) አሸባሪውን ሸኔ በመዋጋት ሂደቱ ከወታዳራዊ ሥራው ባሻገር ሕዝቡ ለምን ተሸከመው የሚለውንም በወጉ እያሰቡ መሄድ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ሂደቱ ወታደራዊና ፖለቲካዊ መንገዱን እያስታረቁ መሄድን ይፈልጋል ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑን ሕዝቡ ለምንድን ነው የተሸከመው የሚለውን መፈተሽና ከመንግሥት ምን አጥቶ ነው የሚለውን እያወቁ መጓዝን ይጠይቃል ነው ያሉት።

የፌደራሉ መንግሥት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመሆን ከፍተኛ ተጋድሎን እየፈፀመ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄም መታወቅ አለበት ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያቸው የሽብር ቡድኑ ሸኔ ጨለማን ተገን እያደረገ ከሃብታም ገንዘብ የሚቀማ፣ ለሰው ልጅ ፍፁም ክብር የሌለውና እየተሽሎከለከ የሚገድል ነው ሲሉ አክለዋል።

የሆነው ሆኖ ትሕነግም ሆነ ሸኔ ወይም ሌላ አካል ኢትዮጵያን ሊያፈርስ እንደማይችል ማረጋግጥ ተችሏል ሲሉም ተደምጠዋል።