ተፈጥሯዊ እና ሰብአዊ ነውጦች ጋር ተያይዞ ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ ናቸው- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – ዓለማችን እየተጋፈጠች ከምትገኛቸው ተፈጥሯዊ እና ሰብአዊ ነውጦች ጋር ተያይዞ፣ ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የገንዘብ፣ እቅድ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች 53ኛ ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

በመክፈቻ ንግግራቸው ዓለማችን እየተጋፈጠች ከምትገኛቸው ተፈጥሯዊ እና ሰብአዊ ነውጦች ጋር ተያይዞ፣ ፈጠራ የታከለባቸው ምላሾች አስፈላጊ መሆናቸው የአጀንዳውን ወቅታዊነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ የኮቪድ-19ን ቀውስ በመጋፈጥ ሂደት ውስጥ የመቋቋም ችሎታዋን ከማሳየት ባለፈ መፍትሄዎችን ለመቅረፅ እና ተግባራዊ ለማድረግ ያሳየችውን አቅም እና ዝግጁነት አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጣይ አቅጣጫዎች በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተኮር ኢኮኖሚ እና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ለትግበራ በሚያመች መንገድ ማብቃት ላይ ማተኮራቸው እጅግ  አስፈላጊ መሆኑ ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡