ጠ/ሚ ዐቢይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ነፃ የንግድ ቀጣና ዞን ስራ አስጀመሩ

ነሐሴ 8/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ የተቋቋመውንና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ዞን” መርቀው ስራ አስጀመሩ።

በዛሬው እለት ምረቃው ዕውን የሆነው “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ዞን” የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ የተለያዩ አልሚዎች ገብተው በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢምፖርትና ኤክስፖርት የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ዞን የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የአገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ላልተው የሚተገበሩበት ሲሆን፣ በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ኩባንያዎች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

በድሬዳዋ የተቋቋመው “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ዞን” ለመጋዘንነትና ለኤክስፖርት ማቀነባበሪያነት የሚያገለግሉ ሼዶች በጥራትና በብዛት ያለው ሲሆን ኢትዮጵያ በቀጠናው ትልቅ ገበያ በመመሥረት ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከመላ ዓለም ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት ላይ የወሳኝት ሚና እንዲኖራት የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጿል።

ነፃ የንግድ ቀጣናው ዕውን መሆን ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፤ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲጎለብት፣ የኤክስፖርት ዕድገት በላቀ ደረጃ እንዲመዘገብና የኤክስፖርት ምርት መጠን በማሳደግ እረገድ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመንትን በመሳብ፤ የዕውቀት ሽግግርን ለማሳለጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታመናል።

ደረሰ አማረ (ከድሬደዋ)