ጠ/ሚ ዐቢይ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ በክላስተር የታረሰውን የስንዴ ማሳ ጎበኙ

ጠ/ሚ ዐቢይ

ጥቅምት 03/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ በመገኘት በክላስተር የታረሰውን የስንዴ ማሳ ጎበኙ።

አከባቢው ከዚህ ቀደም በሴፍት ኔት ድጋፍ የሚተዳደር አከባቢ የነበረ ሲሆን፣ የአከባቢው አርሶ አደር በክላስተር ስንዴ እንዲያመርት መደረጉን ተከትሎ አካባቢው ተስፋ ሊኖረው እንደቻለ ተመልክቷል።

አካባቢው ላይ ያሉ አርሶ አደሮች ከ700 በላይ ሄክታር መሬት በአሁኑ ሰዓት ላይ በስንዴ ዘር እንዲሸፈን ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉብንታቸው ወቅት የስንዴን ምርት የማስፋት ዓላማው ኢትዮጵያን ከልመና ማላቀቅ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን ተሞክሮ ሁሉም ክልሎች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በጉብኝቱ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የሁለቱም ከተማ አስታደር ከንቲበዎች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ከ900 በላይ ሄክታር መሬት በክላስተር ስንዴ የተሸፈነ ሲሆን፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ1.2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ እንዲሸፈን ተደርጓል። ከዚህም ውስጥ ከ800 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ በክላስተር ስንዴ መታረሱ ተጠቁሟል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ልኡካን ቡድን በአካባቢው ላይ የሚያደርገው የመስክ ምልከታ የሚቀጥል ሲሆን፣ በዚህም የተገኙ መልካም ስራዎች እና ድክመቶች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሚልኪያስ አዱኛ