የካቲት 23/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እገዛ እንዲውል 216 ሺህ ብር ትናንት አበረከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘቡን ያበረከቱት ከመጽሐፋቸው ሽያጭና የወር ደመወዛቸውን በመቀነስ እንደሆነ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም ሶስት የውሃ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ቦቴዎችን በማመቻቸት ለጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲደርስ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመወከል ድጋፉን ያስረከቡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ ንጉሴ ናቸው።
ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እቅድና ፋይናንስ ቢሮ አስተባባሪ አቶ ካህሳይ ብርሃኑ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሰረት ከመጽሐፋቸው ሽያጭ 200 ሺህ ብር እና ከወር ደመወዛቸው ደግሞ 16 ሺህ ብር አበርክተዋል።
በክልሉ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት አሁንም ድጋፍ ስለሚያስፈልግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አርአያነት በመከተል ሌሎችም እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ስለትግራይ መልሶ ግንባታ ከክልል ፕሬዝዳንቶችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በበይነ መረብ መምክራቸውን፤ ለዚህም የአንድነት ተግባር ከወር ደመወዛቸውና ከመደመር መጽሐፋቸው ሽያጭ ገንዘብ እንዲሁም በጽህፈት ቤታቸው በኩል ሶስት የውሃ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ቦቴዎችን ማዋጣታቸውን በወቅቱ ይፋ አደርገዋል።
በዚህ ወቅትም ሁሉም ሰው ትግራይን መልሶ በመገንባቱ የአንድነት ንቅናቄ እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።