ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የትግራይ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በጠበቀ መልኩ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደተዋቀረለት ገለጹ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የትግራይ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን በጠበቀ መልኩ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደተዋቀረለት ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከፓርላማ አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ለሕወሓት አመራሮች የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎች እና ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ሽምግልና እንደላኩ ገልጸው፣ ለትግራይ ህዝብ ጦርነትና ግጭት እንደማይገባውና የጁንታው አባል ችግሩን እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡

ሕወሃት ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ ትግራይን ሲመራ በነበረበት ወቅት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን የትግራይ ህዝብ በሴፍቲኔት ሲተዳደር፣ አመራሮቹ ግን ጦር ሰባቂ፤ ችግር ፈጣሪ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

በሰሜን እዝ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ተከትሎ በሕወሃት ታግተው የነበሩ አባላት ሙሉ በሙሉ የማስለቀቅ እና የተሰውትን የመቅበር ስራ መሰራቱን በማብራሪያቸው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳር ጋር በመቀናጀት የክልሉን ሠላም ሙሉ ለሙሉ ለመመለስና ቀሪ ወንጀለኞችን የማደን ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ የትግራይ ሕዝብና ሌሎች ክልሎች በትግራይ ክልል የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳዳር እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የፌዴራል መንግስት ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

(በብርሃኑ አበራ)