ጠ/ሚ ዐቢይ ኢትዮጵያ ለማደግ የምታሳየው ድርጊት ፈተናም እድልም እያመጣባት እንደሚገኝ ገለጹ

ሰኔ 30/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ለዓለም ያላት አስተዋጽኦ እና ለማደግ የምታሳየው ድርጊት ፈተናም እድልም እያመጣባት እንደሚገኝ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት እየተካሄደ ባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 16ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ቀደምት መጻሕፍትና ቅርሶች በመላው ዓለም ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት መገኘቱ የዓለም ማኅበረሰብ ሀገሪቱን ችላ እንዳይላት አድርጓታል ብለዋል፡፡

በዚህም የሀገሪቱን ከፍታ የማይፈልጉ እና ውድቀቷን የሚሹ ኃይሎች ጥፋቷን ለማፋጠን አሽባሪዎችን በመደገፍ ጭምር እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ሀገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ለዓለም መዝባሪ ሀገራት ትኩረት እንድትሆን አድርጓታል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥዎች ካለመገዛት አልፋ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ሀሳብ ጠንሳሽ እና በብዙ መልኩ ረዳት መሆኗ ሌላው የበዝባዥ ሀገራት ራስ ምታት መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፋ እስከ ኮሪያ ድረስ ለዲፕሎማሲ እና ሰላም ማስከበር የተንቀሳቀሰች መሆኗም እንዲሁ፡፡

በዚህም የውጭ ተላላኪ ኃይሎች በሀገሪቱ የእርስ በርስ ፍጅት እንዲኖር እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የሀሰት ዘገባዎችን በመስራት፣ በዲፕሎማሲና እና ኢኮኖሚ ጫና እንዲሁም ተላላኪዎችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ማፍረስ አይችሉም ብለዋል፡፡

እነዚህ ኃይሎች ይህ ሁሉ ሙከራ ካልተሳካላቸው ራሳቸው ጦር በማዝመት ጭምር ኢትጵያን ለማፈራረስ ስለሚጥሩ የመከላከያ ኃይሉን ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከፖለቲካ ጥቅም አስተሳሰብ የጸዳ አድርጎ መገንባት በማስፈለጉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡