ጣቢያው በበጀት ዓመቱ ከ3ሺህ በላይ ጊጋ ዋት በሰዓት ለማመጨት ተዘጋጅቷል ተባለ

ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) – የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ 3ሺህ 248 ጊጋዋት ሰዓት ለማመንጨት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ቢምረው ዳኜ እንደገለጹት፤ የጣቢያው አራቱም ዩኒቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተከናወነው የሚልቅ ኃይል ለማምረት መታቀዱን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የጥገና ባለሙያዎች አቅም እያደገ መምጣቱና ከሀገር ውጪም ሆነ ከማዕከል የጥገና ባለሙያ እስኪመጣ ሳይጠበቅ የሚሰራ ባለሙያ መፈጠሩ፣ዩኒቶች በጥገና ምክንያት ከሥራ ውጪ የሚሆኑበት ጊዜ መቀነሱና የተሻለ የውሃ መጠን በክረምቱ እንደሚኖር ታሳቢ መደረጉ እቅዱን ከፍ አድርጎ ለማቀድ መነሻ ሆኗል ብለዋል፡፡

ጣቢያው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2ሺ 773 ጊጋ ዋት  ኢነርጂ በማምረት የዕቅዱን 90 በመቶ ያሳካ ሲሆን በዓመቱ ከተመረተው ኢነርጂ ውስጥ የ17 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ እንደነበረው ተገልጿል፡፡