ጥምር ሃይሉ ደራሼን ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እየመከረ ነው

ሚያዚያ 28/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳን ወደ ቀደመ ሠላም ለመመለስ የፀጥታ ጥምር ሃይሉ ከአካባቢው ከተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በጊዶሌ ከተማ መምከር ጀምሯል፡፡

በዞን የመደራጀትን ጥያቄ በሃይል ለማረጋገጥ በህገወጥ መንገድ የታጠቁ አካላት በአካባቢው ግጭት በመፍጠር በርካታ የመንግስት ባለስልጣናትና የፀጥታ አካላትን መግደላቸው ይታወሳል።

እነዚህ በህገ ወጥ መንገድ የታጠቁ ሃይሎች በፈጠሩት የጸጥታ ችግር የግለሰቦችና የህዝብ ንብረቶች መዘረፋቸውና መውደማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህን ተከትሎ አካባቢውን ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ የተደራጀው የጸጥታ ጥምር ሃይል በኮማንድ ፖስት አደረጃጀት የማረጋጋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፋዎች ባነሱት ሀሳብ የተፈጸመውን ህገወጥ ተግባር በጽኑ አውግዘዋል።

በህገወጥ ድርጊቱ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።