ጥራት ያላቸው የሕዝብ መገልገያ ህክምና ተቋማትን ማብዛት ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) የህክምና ዘርፍ ስብራቶቻችንን በመጠገን ንፁህና ጥራት ያላቸው የሕዝብ መገልገያ ህክምና ተቋማትን ማብዛት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንፃር የተሻለ እምርታ እያሳየች ቢሆንም በህክምናው ዘርፍ በተቋማቱ የጥራት ችግር በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዘመናዊ የኩላሊት እጥበት ማዕከል በመገንባት ከየአብ ሜዲካል ፋውንዴሽን ባገኘው 30 የኩላሊት እጥበት (ዲያሊሲስ) መሳሪያ ድጋፍ አገልግሎቱን አስጀምሯል።

በአዲስ አበባ በሦስት ማለትም በጳውሎስ፣ በዳግማዊ ሚኒሊክ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት በነጻ ቢሰጥም በመሳሪያ እጥረት የተነሳ በእድሉ መጠቀም የቻሉት ሰዎች ቁጥር ጥቂት መሆኑ ተነስቷል።

በዚህም አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዘመናዊ የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነው ተብሏል።

በደረሰ አማረ