ጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

 

የካቲት 20/2013 (ዋልታ) – ጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ ዓመት 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአዳማ እያካሄደ ነው፡፡

የጨፌው አፈ ጉባዔ ሎሜ በዶ ይህ ጉባዔ የፅንፈኛዉ ህወሃት መቀበር ማግስት እና የኢትዮጵያዉያን የአንድነት ተምሳሌት በሆነዉ የ125ኛ የአደዋ የድል በዓል ዋዜማ ላይ መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ጨፌዉ ትላንትም ሆነ ዛሬ ለሀገር አንድነት ዋጋ የከፈሉ የኦሮሞ ጀግኖችን ያስታዉሳልም ብለዋል።

አፈ ጉባዔዋ እንዳሉት ጨፌዉ የኦሮሞ ህዝብ ከጀግናዉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የፅንፈኛዉ ቡድንን ሀገር የማፍረስ ህልም ሲያከሽፍ ላደረገዉ ድጋፍ እዉቅና ይሰጣል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማርገብ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝንደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለጨፌው ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል፡፡

መንግስት ከውጪ የሚገቡ መሰረታዊ ፍጆታዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከምንግዜውም በላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርም ነጋዴዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ዉስጥ ጠላት የክልሉን ሰላም ለመረበሽ ሲያደርግ የነበረዉ ሙከራ በህዝቡና በመንግስት አንድነት ሊከሽፍ መቻሉንም ነው ፕሬዚዳንቱ የጠቆሙት፡፡

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተሰራዉ ስራ ለፍርድ ቤት ከቀረቡት 25ሺህ 700 የክስ መዝገቦች ዉስጥ ለ18ሺህ 800 መዝገቦች ፍትህ መሠጠት መቻሉን ለጨፌዉ አስረድተዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው የጨፌው መደበኛ ጉባኤ የአስፈጻሚ አካላትን የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ከገመገመ በኋላ በተለያዩ አዋጆች ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
(በሶሬቻ ቀበኔቻ)