ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል

አፈ ጉባኤ ሰኣዳ አብዱረህማን

የካቲት 9/2015 (ዋልታ) የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 2ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በአዳማ ከተማ ማካሄድ ይጀምራል።

ጨፌው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሚቀርበውን የ2015 ዓ.ም የግማሽ በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም በማዳመጥ ይገመግማል ነው የተባለው።

ጉባኤውን አስመልክቶ የጨፌው አፈ ጉባኤ ሰኣዳ አብዱረህማን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የፀጥታና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተወሰዱ እርምጃዎች፣ በክልሉ የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች እና ሌሎች ጉዳዮች በሪፖርቱ በዋናነት የሚመለከቱ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ ረቂቅ ህጎች ይፀድቃሉ ተብሎ የሚጠበቁ ሲሆን ከነዚህም የክልሉን የገጠር ልማት አስተዳደርና አጠቃቀምን እንደገና ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት አስተዳደርን የሚመለከት እና የክልሉን ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አደረጃጀት ስልጣን እና ተግባራቸውን የሚመለከተው ረቂቅ ተጠቃሽ ነው ተብሏል።

ጉባኤው ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይካሄዳልም ነው የተባለው።

በሚልኪያስ አዱኛ