ፀረ-ሰላም ሀይሎችን እኩይ ተግባር ለመመከት ቆርጠን ተነስተናል – የካፋ ዞን ምልምል ወጣቶች

ሐምሌ 25/2013 (ዋልታ) – የሀገራችንን ሉኣላዊነትና የህዝባችንን ሰላም የሚዳፈሩ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን እኩይ ተግባር ለመመከት ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ የካፋ ዞን ምልምል ወጣቶች ገለፁ።

በካፋ ዞን “እኔም ለሀገሬ እዘምታለሁ”በሚል መሪ ሀሳብ ሀገርን ከተቃጠው አደጋ ለማዳን እና መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል የወሰኑ 572 የካፋ ዞን ፈቃደኛ ወጣቶች በቦንጋ ከተማ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

የካፋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ በላይ ተሠማ በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ወጣቶቹ ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው ሀገርን ለማገልገል ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበው የዞኑ ሕዝብና መንግስት በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎናቸው እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በገንዘብ በሞራል እና በአይነት የሚደረገውን ድጋፍ የዞኑ መንግሥትና ህዝብ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ፈቃደኛ ወጣቶቹ በሚዘምቱበት ሁሉ ወታደራዊ ጨዋነትን በመላበስ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ እንዲሆኑም አቶ በላይ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አማካሪ መሠለ ከበደ  በበኩላቸው ወጣቶች በሀገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተው በፍላጎታቸው ለሀገራቸው ደጀን ለመሆን በመወሰናቸው የተሠማቸውን አክብሮት ገልጸዋል።

የአባቶቻቸውን የአሸናፊነት ገድል በመድገም ሀገርን ሊበትን የመጣውን የህወሀት ጁንታ ቡድን ለመደምሰስ ያሳዩት ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ሀገራችንን የሚያኮራና በታሪክ ሲታወስ የሚኖር አኩሪ ተግባር ነውም ብለዋል።

ፈቃደኛ ወጣቶቹ በሰጡት አስተያየት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንዳርጋለን ብለው በተለይም ሀገራችንን ብሎም የትግራይ ህዝብን እንቅልፍ እየነሳ የምገኘውን አሸባሪ ቡድን ለማጽዳት በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ በመሳተፋቸው እልህና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

ወጣቶቹ አክለውም እኛ ወጣቶች እያለን ሀገራችን የአሸባሪዎች፣ የጁንታዎች እንዲሁም የፀረ-ሰላም ሀይሎች መፈንጫ አትሆንም፣ የሀገራችን ዳር ድንበር በምንም እንዲደፈር አንፈቅድም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በአሸኛኘቱ ላይ ከካፋ ዞን ወጣቶች ባሻገር የሸካ ዞን የሀገር ምልምል ወጣቶችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በሽንት መርሃ ግብሩ ላይ የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የካፋ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ለዘማች ወጣቶች የኢትዮጵያን ሠንደቅ አላማ አስረክበዋል፡፡

(በነስረዲን ኑሩ)