ፅንፈኝነትና አክራሪነት በጋራ በመከላከል ለሀገር ልማት መሰለፍ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሰኔ 30/2014 (ዋልታ) ፅንፈኝነትና አክራሪነት በጋራ በመከላከል ለሀገር ልማት መሰለፍ ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በክልሉ የሚገኙ ጥምር የፀጥታ አካላት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ያካሄዱ ሲሆን በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በመቀናጀት በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ሰላም እንዲጎለብት በቁርጠኝነት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። በዚህም በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የብሔር ፅንፈኝነትን እና የሃይማኖት አክራሪነትን በጋራ በመከላከል የሀገሪቱ ልማት እንዲረጋገጥ በጋራ መቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቄላ ሁሪሳ (ፒኤችዲ) በእለቱ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የፀጥታ አካላት ተሰባስበው ችግኝ መትከላቸው ለአንድ ዓላማ መቆማቸውን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የፀጥታ ኃይሉ ለሀገሪቱ ሰላምና የህግ የበላይነት መከበር በቁርጠኝነት እየሰራ ከመሆኑም ባለፈ ለሀገሪቱ ልማት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን በልማቱም በንቃት እየተሳተፉ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።

የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ከማስቻል አንፃርም ተገቢውን ክትትልና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

በክልሉ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በችግኝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ የክልሉ የፀጥታ አባላትና አመራሮች ተገኝተዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)