ፈተናዎች ለመሻገር የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የመረጃ ፍሰትና ስርጭትን መከወን ይጠበቅበታል ተባለ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ለመሻገር በምታደርገው ጥረት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የተቀናጀና መዋቅራዊ ሂደቱን በጠበቀ አግባብ የመረጃ ፍሰትና ስርጭትን መከወን እንደሚጠበቅበት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ፍትሕና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕፀገነት መንግስቱ እና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔው የ2014 የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እንዲሁም የክልልና የፌዴራል ተቋማት ስራ ዘመን አፈፃፀምና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ለውይይት እንደሚቀርብ ተገልጿል።

በዛሬው መርኃ ግብርም በቀጣይ 5 ዓመታት ገቢራዊ የሚደረገው የአምስት ዓመት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

ሚኒስትሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጣዊና ውጫዊ መልከ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁማ በኢኮኖሚው መስክ በስኬት መሻገሯን የሕዳሴ ግድብን፣ አረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ ስንዴ ምርትና ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ስኬትን ለአብነት አንስተዋል።

የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በአዲስ አደረጃጀት ዘግይቶ የተቋቋመና የራሱ ውስንነቶች ቢኖሩትም ባለፉት 10 ወራት የመንግስትን መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ ረገድ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተሻለ ስራዎች ስለመከናወናቸው አንስተዋል።

የኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ በመረጃ ስርጭት ረገድ የተናበበና የተቀናጀ አግባብ መረጃን መጋራት ላይ መስራቱን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በሰላም ለመቋጨት መንግስት የሰላም እጅ ቢዘረጋም ባንዳዎችና ፀረ ሰላም ኃይሎች የሰላም ጥሪውን እያደናቀፉ ስለመሆኑ አንስተዋል።

አገራዊ የሰላም ችግሩን በሰላም ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ መረጃ በማቅረብ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በተናበበ፣ ወጥነትና ብዝሀነትን በጠበቀ፣ በተቀናጀና መዋቅራዊ ሂደቱን በጠበቀ አግባብ የመረጃ ፍሰት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፣ለዚህም አንድ አገራዊ አጀንዳዎች ያሉት የኮሙኒኬሽን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ለዚህም ዘርፉ የሚጠበቅበትን አገራዊ ሚና እንዲወጣ የ5 ዓመት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ስትራቴጂ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልፀው የዕቅዱ አላማ መረጃን በተማከለ፣በፍጥነትና በጥራት ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ዕቅዶች እንደ አገሪቷ ሁናቴ ተለዋዋጭነት ስላለው በየወቅቱ እየተከለሰ እንደሚቃኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፌዴራልና የክልል የዘርፉ ተቋማትም ለዕቅዱ ስኬትና የሚጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መምከርና መወሰን እንደሚጠበቅባቸው ገልፀው፤ መሰል ጉባዔዎችም ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አክለዋል።