ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለቻይና የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የቻይና የመከላከያ ሰራዊት የተመሰረተበትን 95ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ባስተላለፉት መልዕክት የቻይና የመከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሉአላዊነት፣ ፀጥታና ጥቅም ከማስከበር አልፎ ለዓለማችን ሰላምና መረጋጋት እያደረገ ላለው በጎ ሚና ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

ቻይናና ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በመመስረት በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ ትምህርት እና ጤና መስኮች ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መምጣቱን አመላክተዋል።

ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በወታደራዊ ዲፕሎማሲና ትብብር ላይ ከፍተኛ ዕድገት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ አገራቱ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራም እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW