ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አየር ኃይል የሠራዊታችን አንዱ ክንድ ነው አሉ

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የካቲት 20/2014 (ዋልታ) አየር ኃይል የሠራዊታችን አንዱ ክንድ ነው ሲሉ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

መከላከያ በተለያዩ ክንፎች የተደራጀ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አየር ኃይሉን ከቀደመው አቋሙ በተሻለ መልኩ ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአፍሪካ እንደ ተምሳሌትነት ሲወሰድ የነበረውን አየር ኃይልን ላለፉት 27 ዓመታት ማሰልጠን እንዳይችል ተደርጎ እንዲንኮታኮት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን የማዳከም አካሄድ ነበር ብለዋል፡፡

አሁን የሰራዊቱን ቁመና ለመገንባት እንዲቻል አየር ኃይልን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ተቋማት ግንባታና ለውጥ ማከናወን እንደተቻለ አክለዋል፡፡

አየር ኃይል ቀድሞ ከነበረው አቅም የበለጠ ማደራጀት የተቻለና በአኅጉሪቱ ተምሳሌት ለማድረግ የተሄደበት ርቀት አበረታች ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚያስከብር አየር ኃይል በስትራቴጂ እንዲመራ ለማድረግ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

በየአካባቢው በብሔር ውስጥ ተደብቀው እንደ ወያኔ ሀገርን ለመበታተን የሚሰሩ አካላትን የመለየትና የማጥፋት ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡

ይህም በመከላከያ ሠራዊት መጠናከር ላይ የተመሠረተና በዜጎች ድጋፍ የሚረጋገጥ እንደሆነ አንስተዋል።

በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሜዳይ ማልበስ ለአየር ኃይሉ ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለተመራቂ የሠራዊቱ አባላትና ተሸላሚዎች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሰለሞን በየነ