ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያን በውክልና ጦርነት ለማዳከም የሚፈልጉ ኃይሎችን ሴራ ሕዝቡ ሊገነዘብ ይገባል አሉ

ሰኔ 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን በውክልና ጦርነት ለማዳከም የሚፈልጉ ኃይሎችን ሴራ ሕዝቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳሰቡ።

የ8ኛ ዕዝ በግዳጅ አፈፃፀማቸው ብልጫ ላሳዩ የሠራዊት ክፍሎችና አባላት የሜዳይ እና ዕውቅና መስጠት ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል።

በመርኃ ግብሩ ላይ ሽልማት በመስጠት የሥራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት የጥቁር አንበሳ ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚውና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሸባሪው ሕወሓት ባልዋለበት ገድል ራሱን የሚያፅናና ውጊያን ሲያንቆለጳጵስ የሚውል ኃይል መሆኑን ገልፀው በበርካታ አውደ ውጊያዎች የደረሰበትን ሽንፈትና ኪሳራ ግን ማንሳት አይፈልግም ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በርካታ የውጭ ኃይሎች ሀገራችንን ለማዳከም ሰፊ የውክልና ጦርነት አውዶች መክፈታቸውን አንስተው የነዚህን ኃይሎች ሴራ ሕዝባችን በመገንዘብ ሊያከሽፈው ይገባል ብለዋል።

8ኛ ዕዝ አሸባሪውን የትሕነግ ኃይል ለመደምሰስ በታቀደው ዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ የሰራዊታችን ጠንካራ ክንድ በመሆን በቡድኑ ላይ ከፍተኛ የመመከትና የመደምሰስ ሥራውን ሰርቷል።

የዕዙ የሰራዊት አመራርና አባላት በፈፀሙት ገድል ሀገር ከተደቀነባት የመፍረስ አደጋ መታደግ በመቻላችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡