ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሞሮኮ ወታደራዊ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ

ሐምሌ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) የኤፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮው ምክትል ኢንስፔክተር ጀኔራል ስታፍ ሜጄር ጄኔራል አዚዝ ኢድሪሲ ከተመራውን ወታደራዊ ልዑካን ቡድን ጋር በልዩ ልዩ ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ከዚህ በፊት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንደነበርና በተለያዬ ምክንያት ግንኙነቱ ተቋርጦ የቆየ መሆኑን አውስተው አሁን የተዘጋውን በር ከፍተን አዲስ የግንኙነት መስመር ለመዘርጋት ውይይት እና ጉብኝት ማድረጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ መሪ ሜጄር ጀኔራል አዚዝ እድሪሲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚችል ጠንካራ ወታደር ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ጉንኝቱን ለማድረግ መወሰናቸውን  ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በአዲስ መልክ  ለማደስ ከማስቻሉም ባሻገር በሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት በር እንደሚከፍት ጠቅሰዋል፡፡

ካሁን በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በሞሮኮ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በሚቀጥሉት ተከተታይ ቀናት የሞሮኮው ወታደራዊ ልዑክም በተቋሙ የተለያዩ ክፍሎች በመዘዋወር ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

ከጉብኝቱና በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካካል ለሚደረገው ወታደራዊ ስምምነት እና የአፍሪካዊ ወንድማማችነት መንፈስ ታላቅ መሰረት ለመጣል እንደሚያግዝ የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ መግለጻቸውን ከመከላከያ የማህበራዊ የትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።