ፊቼ ጫምበላላ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ እድገት ያለው አስተዋፅኦ የጎላ ነው – ደስታ ሌዳሞ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) የፊቼ ጫምበላላ በዓል ለኢትዮጵያ አንድነት እና ዘላቂ እድገት ያለው አስተዋፅኦ የጎላ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ።
የጫምበላላ በዓል ዋዜማ የሆነው የፊቼ ፊጣራ በዓል በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሠ መሥተዳድር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባለፉት 2 ዓመታት በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ማክበር ሳይቻል መቅረቱን አንስተዋል፡፡
የፊቼ ጫምበላላ በዓል የእርቅና ሰላም እሴትን በውስጡ የያዘ በመሆኑ የበዓሉን እሴቶች ለትውልድ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በዓሉ የኢትዮጽያን አንድነትም ከማጠናከር አንፃር የጎላ አስተዋፅኦ አለው ያሉት ርዕሠ መሥተዳድሩ የበዓሉን እሴቶች በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ጭምር በማካተት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልም ገልፀዋል።
በዓሉ በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ በመመዝገቡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊጠብቀው እንደሚገባ ገልፀዋል።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንደ ክልል ከተዋቀረ በኃላ በዓሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በአደባባይ የሚከበረው።
በሀይሉ ጌታቸው (ከሀዋሳ)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!