ሰኔ 11/2013 (ዋልታ) – ከሶስት ቀናት በፊት የፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ ለአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያቀረቡት ሪፖርት ኃላፊነት የጎደለው፣ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ያልተከተለና ከቅኝ ገዢነት የመነጨ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአውሮፓ ህብረትን በመወከል በኢትዮጵያ የጥቂት ጊዜ ቆይታ ያደረጉት የፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ ባቀረቡት ሪፖርት ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው “ፔካ ሃቪስቶ መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራ የሚያጣጥልና በሐሰተኛ መረጃዎች የተመሰረቱ ሪፖርቶችን፣ ውሸቶችን በማቅረብ ተገቢ ያልሆኑ ጣልቃ ገብነቶች እንዲኖሩ አድርጓል” ብሏል።
ይህም ግለሰቡ በነበራቸው አጭር ቆይታ የተሟላ መረጃ ባለመያዝና ከቅኝ ገዥነት አስተሳሰብ በነመጨ አሳብ የተሰሳተ መረጃ ማቅረባቸውን ነው የገለጸው።
በዚህም ሚኒስቴሩ በፔካ ሃቪስቶ ህወሃትን እንደ ተፎካካሪ አካል ተደርጎ የቀረበውን መረጃ ህወሃት የሽብር ቡድን መሆኑን በመጥቀስ ውድቅ አድርጎ፤ ሕግ ማስከበር ዘመቻውም የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግታትና አባላቱን ለህግ ለማቅረብ የተካሄደ መሆኑንን አስታውቋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ወሳኝ መነሻ መሆኑን ገልጿል።
በግለሰቡ የክልሉ አርሶ አደሮች የክረምት ግብርና ስራዎች ማካሄድ አልቻሉም የሚለው ሪፖርት መንግስትና አጋር አካላት ለአርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ማሰራጨታቸውን ያልዳሰሰ መረጃ መሆኑን በመግለጽ ሪፖርቱን ውድቅ አድርጎታል።
ከዚህ በተጨማሪም ፔካ ሃቪስቶ ከፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን አውስቶ፤ የቀረበው ሪፖርት ግን ሃሰተኛና የተካሄዱ ሰፋፊ ውይይቶችን ያላካተተ መሆኑን አስታውቋል።
ይህም ኃላፊነት የጎደለው፣ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ያልተከተለና ከቅኝ ገዢነት የመነጨ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ሆኖም መንግስት ሉዓላዊነትን በጠበቀ መልኩ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና አጋርነት ችግሮችን በማለፍ እንደሚቀጥል ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል።