ፋብሪካው ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የኩላሊት ማጠቢያ ማሽኖችን አበረከተ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን 2 የኩላሊት እጥበት ማሽኖችና ተንቀሳቃሽ የውኃ ማጣሪያ ማሽን አበረከተ።
በርክክቡ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና የፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ወገኖች ተገኝተዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ሆስፒታሉ በሳምንት ለ40 ያክል የኩላሊት ህሙማን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው ፋብሪካው ያበረከተው የማሽን ድጋፍ በጽኑ ህሙማን ክፍል ያለውን የህክምና አገልግሎት ለማሳለጥ ይረዳል ብለዋል።
ሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመንና የህሙማንን እንግልት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፋብሪካው በተመሳሳይ በጎንደርና አካባቢው የትምህርት ተቋማትን ለማጠናከር የሚካሄደው ጥረት ግቡን እንዲመታ የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለጎንደር ከተማ ሰላምና ልማት ማኅበር አበርክቷል።
ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ከተመሰረተ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ለማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፎች ማበርከቱን የፋብሪካውን መረጃ ጠቅሶ አሚኮ ዘግቧል።