ፋብሪካው ለፋሲካ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት 7 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) የባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ የሆነው ፊቤላ የዘይት ፋብሪካለፋሲካ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት 7 ሚሊየን ሊትር ዘይት ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለገበያ ያልቀረቡ ባለ 10 እና 15 ሊትር ዘይት ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ነው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው ያስታወቁት።
ፊቤላ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ በ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባ የዘይት ፋብሪካ ነው።
በቀን ከ 700 ሺሕ ሊትር በላይ ዘይት እያመረተ የሚገኝ ሲሆን በኃይል መቆራረጥ ምክንያት በሙሉ አቅሙ እያመረተ እንዳልሆነም ተገልጿል።
የዘይት ፋብሪካው ከ1 ሺሕ 200 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉም ነው የተመላከተው።