ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አ.ማ በደብረ ብርሃን ከተማ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጧል።
ፋብሪካው ትምህርት ቤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከአማራ አቀፍ ልማት ማህበር እና ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ታውቋል።
በመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር (አልማ) ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ፈንታ ዳሽን ቢራ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ የልማት አጋር ተቋም ነው ብለዋል።
ለትምህርት ቤቱ ግንባታ 20 ሚሊየን ብር ወጪ ይደረጋል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚሸፍን ተጠቁሟል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአንደኛ ደረጃ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የዘርዓያዕቆብ ትምህርት ቤት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትነት ከፍ እንደሚያደርግ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ለዋልታ የላከው መረጃ ያመለክታል።