ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – ፋይናንሽያል ታይምስ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጣው ዘገባ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የግጭቱ ጠንሳሽ መሆኑን ያላሳየ፣ የተኩስ አቁሙን በመጣስ ህጻናትን ሳይቀር ወደ ጦርነት ማስገባቱን እና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የማያሳይ መሆኑ ተገለጸ።
ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወቃል፡፡
ፋይናንሽያል ታይምስ የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጣውን ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ አስመልክቶ በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ጉዳዮች ኮሚቴ የተቃውሞ ደብዳቤ ለተቋሙ ጽፏል።
ኮሚቴው በደብዳቤው እንዳመለከተው ድርጅቱ ባወጣው ዘገባ ሰብአዊ ድጋፍና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ለመንግስት ያቀረበውን ጥያቄ ለምን ለአሸባሪው የህወሃት ድርጅት አላቀረበም ሲል ሞግቷል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን በጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ግጭቱን እንደጀመረ ለምን በዘገባው አልተካተተም ሲልም ጠይቋል።
መንግስት በቅርቡ የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ቡድን ተኩስ አቁሙን ሲጥስና ወደ አጎራባች ክልሎች ጥቃት ሲሰነዝር ለምን በዘገባችሁ አላካተታችሁም ሲል አመልክቷል።
የሽብር ቡድኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት ሲያስገባና አለም አቀፍ ህግን ሲጥስ የምርመራ ዘገባችሁ በዚህ ላይ ለምን ጥያቄ አላነሳም በማለት ሞግቷል።
ምዕራባውያን በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ላለቸው ፍላጎት ወሳኝ ቀጠና በሆነው አካባቢ ላይ ለአንባቢዎች ሚዛናዊ ዘገባ ሊደርሳቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጾ፤ የተሳሳተና ሚዛናዊ ያልሆነውን ዘገባ ፋይናንሽያል ታይምስ እንዲያርመው ጠይቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።