ፌደራል ፖሊስ ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ መሰማራቱን ገለጸ

ነሐሴ 20/2014 (ዋልታ) የፌዴራል ፖሊስ በአዲስ መንፈስ በበለጠ ተነሳችነትና አንድነት ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ መሰማራቱን ገለጸ፡፡

ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን በ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የተቋሙ አመራርና አባላት የሀገርን ደህንነትና የዜጎችን ሰላም በጀግንነት በማስጠበቅ ረገድ ታላላቅ ስኬቶችን አስመዝግበዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሽብር ቡድኖችን የጥፋት መረብ በመበጣጠስ እና ሴራቸውንም በማክሸፍ መስዋዕትነት ጭምር እየከፈሉ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ፖሊሳዊ ተልዕኮውን በታላቅ ጀግንነት መወጣታቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልፀዋል።

በሽብርተኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንደለበት በውይይቱ በአጽንኦት መነሳቱን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የተቋሙ አመራርና አባላት በ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረጉ በኋላ ዕቅዱን በማፅደቅ በአዲስ መንፈስ በበለጠ ተነሳችነትና አንድነት ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ መሰማራታቸው ተገልጿል፡፡