ግንቦት 28/2014(ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባደረገው ሪፎርም በአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርገውን የቴክኖሎጂ ትጥቅ የታጠቀ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊት ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስታወቁ።
” በመስዋዕትነታችን የሀገራችን አንድነትና የሕዝብ ሰላም ይረጋገጣል!” በሚል መሪ ሀሳብ የምስጋና እና ዕውቅና መርኃ ግብር እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመርኃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት 80 ዓመት የሞላው የፖሊስ ተቋም በአገር ኅልውና ዘመቻዎች ከመከላከያ እና ከክልል ፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አኩሪ ገድልን ፈፅሟል ብለዋል።
በተቋሙ ተልዕኮ የላቀ ሥራ አፈፃፀም የበለጠ ለማሳደግ ዕውቅና መስጠትና ምስጋና ማቅረብ የበለጠ ሞራል ስለሚፈጥር ዓመታዊ የፖሊስ ቀን መርኃ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በዓውደ ግንባሮች ጀግንነት የፈፀሙ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የግልና የቡድን ጀግኖችና የሥራ ክፍሎች የጀግና እና የላቀ ጀግና ሜዳይ እና የሰርተፊኬት ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በጦርነቱ የተሰው አባላትም ይመሰገናሉ ነው ያሉት።
የዛሬው መርኃ ግብር ማስጀመሪያ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም በክልል ጠቅላይ መምሪያዎ ይቀጥላል ብለዋል።