ፓርቲው በሕዝብ መድረክ የተነሱ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ወደ ተግባር መግባቱን ገለጸ

መጋቢት 30/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ  ጽሕፈት ቤት ከሕዝቡ ጋር ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች ሕዝቡ በግልፅነት ያነሳቸውን በአጭር ጊዜ መመለስ ያለባቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገለጸ፡፡

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከህዝቡ ጋር ሲደረጉ በነበሩ ውይይቶች  ህዝቡ በግልፅነት ያነሳቸውን  በአጭር ግዜ መመለስ ያለባቸውን አንገብጋቢ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ልዩ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በየመድረኮቹ ቃል በገባው መሰረት በፍጥነት  በህዝብ መድረኮች የተነሱት አግባብነት ያላቸው በአጭር ግዜ መመለስ ያለባቸውን   ጥያቄዎች በሙሉ አንድ በአንድ ተለቅመው በእቅድ እንዲመለሱ ለማድረግ የቀሪ ሶስት ወራት የክልሉ እቅድ በመከለስ አመራሩ የማስተባበር እና የመምራት ሃላፊነት ተከፋፍሎ በሚከተለው  አቅጣጫ  ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በዚሁ መሰረት:-

  1. ሰው ሰራሽ የገበያ አቅርቦት ችግር እና የዋጋ ንረት ከወቅታዊ የኑሮ ውድነት ማቅለል አንፃር የታቀዱትን ተግባራት መከታተልና ውጤታማ ማድረግና በአጠቃላይ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን የሚያስተባብሩትና የሚመሩት።

2.የመንግስት ተቋማትን ስራ ሰአት ፣ አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ ለእንግልት፣ ለሌብነት እና ለግል ተጠቃሚነት አመራሩን ለማግኘት እንቸገራለን የሚባለውን ችግር ለመቅረፍ በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደግሞ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፈሪሃ መሀመድ የሚያስተባብሩት የሚመሩት።

3.ከከተማ ግብርና ዘርፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መከታተልና ውጤታማ ማድረግን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የግብርና ልማት ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሚስራ አብደላ ሚያስተባብሩት የሚመሩት።

  1. ከገጠርና ከተማ ልማት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና ከፕሮጀክቶችን መከታተልና ውጤታማ ማድረግን የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አሚና አብዱልከሪም የሚያስተባብሩት የሚመሩት።

5.ስርዓት አልበኝነት ከመቆጣጠርና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ  አንፃር የሀረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ የሚያስተባብሩትና የሚመሩት ግብረ ሃይል ወደተግባር ገብቷል።

6.ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ከስራ እድል ፈጠራና ተያይዞ ለተነሱ ጉዳዮች ለመቅረፍ  ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዞች ማስፋፊያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሰሚራ ዩሱፍ የሚያስተባብሩት የሚመሩት።

7.ከፖለቲካ እና ከአስተዳደራዊ እርምጃ በሚያልፉጉዳዮች ላይ የሚሰማራ የወንጀል ጉዳዮች አጣሪ ጊዚያዊ ግብረ ኃይል የሚያጣራ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም የሚያስተባብሩት የሚመሩት።

ከህዝብ ቅሬታ መፍታት ጋር ተያይዞ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ በሳምንት ሶስት ቀናት ማለትም ሰኞ ፣ እሮብና አርብ ሙሉ ቀን የትኛውም አመራር ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ ለህዝቡ  አገልግሎት እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፎ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

የክልሉ መንግስት መደበኛ ስራዎች በታቀደላቸው መሰረት የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች ፓርቲው የወሰናቸውን ውሳኔዎች ከግብ እንዲደርስ የተለመደውን ድጋፉን ሳይቆጥብ ሊያበረክትና ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት ሊረባረብ ይገባል፡፡

የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት

መጋቢት 30/2014 ዓ.ም

ሐረር