ፓርቲው ከ268 ሺሕ በላይ አባላት እና አመራሮቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ

ሐምሌ 25/2014 (ዋልታ) ብልጽግና ፓርቲ “ፓርቲው የሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት አልተወጡም” ባላቸው ከ268 ሺሕ በላይ አባላት እና አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
የፓርቲው የአደረጃጀት ዘርፍ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እና የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያዘጋጀው አገር አቀፍ ጉባኤ ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል።

የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ካሊድ አልዋን ብልጽግና ፓርቲ ከ12 ሚሊዮን በላይ አባላትና አመራሮች እንዳሉት ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ10 ሚሊዮን 15 ሺሕ 336 የፓርቲው አባላት እና አመራሮች ላይ የማጥራት ተግባር መካሄዱን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ፓርቲው ያስቀመጠውን አቅጣጫዎች፣ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት ባልተወጡ 268 ሺሕ 251 አባላትና አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

እርምጃው የተወሰደባቸው አባላትና አመራሮች የስነ ምግባር፣ የአመለካከትና የአፈጻጸም ችግሮች ያሉባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከነዚህም ውስጥ የሕዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ያልመለሱ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ የሚገኙ ከ33 ሺሕ የሚበልጡ አመራሮች ይገኙበታል ብለዋል።

በእነዚሁ አካላት ላይ የተግሳጽ፣ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የማሸጋሸግ እና ከኃላፊነታቸው የማንሳት እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ፓርቲው ኃላፊነታቸውን በማይወጡ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባና የአስተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን በድሬዳዋ እየተሰሩ የሚገኙት የልማት ስራዎች የፓርቲውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ከልማቱ ጎን ለጎን የአስተዳደሩን ነዋሪዎች ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ፣ በጸጥታና ሕግ የማስከበር ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ አገር አቀፍ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ይቆያል።