ፓርቲው የተጀመረውን ሁሉን ዐቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እሰራለው አለ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን ዐቀፍ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ የፓርቲው አንደኛ ጉባኤ “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
“ብልጽግና የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ተከትሎ የመጣ ለውጥ የወለደው ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነው” ሲሉም አብራርተዋል።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት ፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤውን ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያካሂድ መወሰኑን አመልክተዋል።
የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የማሸጋገር ዓላማን የሰነቀ መሆኑንም አብራርተዋል።
የለውጥ ሂደቱን በጥልቀት መገምገም፣ የተገኙ ስኬቶችን ጠብቆ ማስቀጠል፣ የታዩ ድክመቶችን ማረም እንዲሁም የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የጉባኤው ትኩረት መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ፓርቲውን በብቃት የሚመሩ አመራሮች ይመረጣሉ ሲሉም ጠቁመዋል።
በጉባዔው 1 ሺሕ 600 የፓርቲው አባላት በድምጽ፤ 400 የሚሆኑ ተጋባዥ እንግዶች ደግሞ ያለ ድምፅ ይታደማሉ ብለዋል።
በጉባኤው ላይ ከ38 የተለያዩ አገራት የሚጋበዙ 41 የብልጽግና እህት ፓርቲ ተወካዮችም ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችም በጉባኤው እንደሚሳተፉ ኢዜአ አስነብቧል፡፡